የዳያስፖራ አባላት በመዲናዋ ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ በቂ ዝግጅት ተደርጓል
********************************
ወደ አገር ቤት የገቡ የዳያስፖራ አባላት በሚንቀሳቀሱባቸው ሥፍራዎች ሁሉ የጸጥታ እና ደህንነት ስጋት እንዳይገጥማቸው ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
‘የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት’ ጥሪ ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት በመግባት ላይ ናቸው።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ የዳያስፖራ አባላቱ በመዲናዋ ያለ ምንም ስጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ፖሊስ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ከአየር መንገድ ጀምሮ በሚያርፉባቸው ሆቴሎች፣ በመዝናኛ ቦታዎች፣ በንግድ ማዕከላት፣ በትራንስፖርት እና ሌሎች ሥፍራዎች ሳይታወኩ እንዲንቀሳቀሱ የጸጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
በአዲስ አበባ የጸጥታ ሥራው ተጠናክሮ እንደቀጠለ የገለጹት ኮማንደር ፋሲካ፤ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ወደሚኖርበት አገር ሲመለስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውነታውን በማሳወቅ አምባሳደር እንዲሆንም ይፈለጋል ብለዋል።
ይሁንና አጋጣሚውን ተጠቅመው ዳያስፖራው ላይ ዝርፊያና መሰል ህገ-ወጥ ተግባር ለመፈጸም የሚሞክር ቢኖር ኮሚሽኑ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
Via: EBC